Monday 6 August 2012

ስለ እግዚአብሔር ፍቅር

ስለ እግዚአብሔር ፍቅር

ሀ. ፍቅር ምንድን ነዉ? የተለያዩ የፍቅር ዓይነቶች
በብሉይ ኪዳን ፍቅር ተብሎ የተተረጎመዉ አሄብ(aheb) የሚለዉ ዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ላቭ(Love) እንደሚለዉ የእንግሊዝኛዉ ቃል ሁሉ አንዱ ቃል የስፋ ትርጉም ይዟል፡፡ ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ግን ፍቅር ተብሎ የተተጎመዉ የተለያዩ ቃላት ሲሆን እነሱም፡-
1. ስቶርጌ (storge)፡- ተፈጥሮአዉ የሆነዉንና በእናትና በልጅ መካከል ያለዉን የፍቅር ግንኙነት ያመለክታል፡፡
2. ፊሊያ(philia)፡-በጓደኛሞች መካከል ያለን ፍቅር ያመለክታል፡፡
3. ኢሮስ(eros)፡- በትዳር ጓዳኛሞች መካከል ያልን ፍቅር ግንኙነት ያሳያል፡፡
4. አጋፔ(agape)፡- ግን ከላይ ከተዘረዘሩት ሁሉ የተለየ ሲሆን መለኮታዊ የሆነዉን የእግዚአብሔርን ፍቅር ያመለክታል፡፡ ይህም ራስን መስጠት ያለበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ፡፡

ከላይ ከተራ ቁጥር 1-3 ያሉት ፍቅር ተብለዉ የተተረጎሙት ቃላት ሁሉ ተፈጥሮአዊ ሲሆኑ አጋፔ የሚለዉ ግን መለኮታዊ የሆነዉን ፍጹም ፍቅር የሚያመለክት ይዘት ያለዉ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን ከላይ ከተራ ቁጥር 1-3 ያሉትም የፍቅር ዓይነቶች በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ቢሆኑም በዉድቀት ምክንያት ሰዎች በተሳሳተና በተዛባ መልኩ እንዲሁም ራስ ወዳድነት በተሞላበት ሁኔታና መንገድ ሲጠቀሙባቸዉ ይታያል፡፡
አጋፔ ፍቅር ግን ከሌሎቹ የፍቅር ዓይነቶች የተለየና ከራስ ወዳድነት በወጣ ሁኔታ መለኮታዊና ፍጹም የሆነዉን የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያመላክት ነዉ፡፡ እግዚአብሔርም በእኛ ዉስጥ እንዲታይና እንዲኖር የሚፈልገዉ ይህንኑ የፍቅር ዓይነት ነዉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በስፋትና በተደጋጋሚ የሚዳስሰዉ ስለዚህ የፍቅር ዓይነት ነዉ፡፡
ለ. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር የሚያስተምረን ምንድን ነዉ?
መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስለ ፍቅር በስፋት ያብራራል/ያስተምራል፡፡
ፍቅር በብሉይ ኪዳን
እግዚአብሔር አምላክ እስራኤልን ስለወደደዉ የተለየ ሕዝብ አድርጎ እንደመረጠዉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ኦሪት ዘዳግም ም.4 ቀ.37፣ ም.10 ቁ.15፣ ትንቢተ ኢሳይያስ ም.43 ቁ.1-4 በሌላ በኩል ደግሞ እስራኤል ጌታ አምላኩን በፍጹም ልቡ በፍጹም ነፍሱ በፍጹም ኃይሉ እንዲወድ ታዟል፡፡ ኦሪት ዘዳግም ም.6 ቁ.4-5 ይህም ፍቅር እግዚአብሔርን በማገልገልና ትዕዛዙን በመፈጸም የሚገለጽ ነበር፡፡ ኦሪት ዘዳግም ም.10 ቁ.12-13 እና መጽሐፈ ኢያሱ ም.22 ቁ.5
እግዚአብሔርን ከመዉደድ ባሻገር እስራኤል ባልንጀራዉን እንደራሱም እንዲወድ ታዟል፡፡ ኦሪት ዘሌዋዉያን ም.19 ቁ.18፣ በዘፍጥረት ም.24 ቁ.67፣ ም.29 ቁ.18-20፣ ኦሪት ዘዳግም ም.7 ቁ.9፣ 1ኛ ሳሙኤል ም.18 ቁ.20፣ 2ኛ ሳሙ. ም.13 ቁ.1 መዝሙረ ዳዊት ም.31 ቁ.23፣ ትንቢተ ዳንኤል ም.9 ቁ.4
ፍቅር በአዲስ ኪዳን
በአዲስ ኪዳን ፍቅር ተብለዉ የተተረጎሙ ሁለት ቃላት ያሉ ሲሆን እነሱም፡- አጋፔና ፊሊያ ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጂ አጋፔ ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በአዲስ ኪዳን ዉስጥ በስፋት የተብራራና ክርስቲያን ሁሉ እንዲኖረዉ በተደጋጋሚ የሚያስተምረዉ የፍቅር ዓይነት ነዉ፡፡
አጋፔ ፍቅር ለወደዱት አካል ቸርነት፣ መልካም ፍቃድ፣ ከበሬታን፣ ግድ ባይነትን የሚያሳይ የፍቅር ዓይነት ነዉ፡፡ ስሜታዊ ከሆነዉ የፍቅር መገለጫ ፊሊያ በተለየ መልኩ ወዶና ፈቅዶ በዓላማ የሚያንፀባርቁት የፍቅር ዓይነት ነዉ፡፡ በአዲስ ኪዳን ፍቅር የሚለዉ ቃል በተጠቀሰባቸዉ በሁሉም ሥፍራች ማለት ይቻላል ይኸዉ የፍቅር ዓይነት አጋፔ(Agape)ነዉ በስፋት ተጠቅሶ የምናየዉ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዩሐንስ ወንጌል ም.21 ቁ.15-17 ስለ ጴጥሮስ ከእነዚህ ሁሉ ይልቅ ትወደኛለህን? ብሎ ሲለዉ ይህንን አጋፔ (ራስ ወዳድነት የማይንጸባረቅበትን) ፍቅር ነዉ የጠየቀዉ፡፡ (ሉቃስ ወንጌል ም.6 ከቁጥር 32-36) በመሆኑም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ማለት በተግባር የሚገለጽ እንክብካቤ ማለት ነዉ፡፡ ፍቅር የሚሰማን ስሜት ሳይሆን በተግባር የምናደርገዉ ነዉ፡፡
ሐ. የፍቅር ምንጭ ምንድን ነዉ?
መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር ምንጭ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አስረግጦ ይናገራል፡፡ 1ኛ. ዩሐ. ም.4 ቁ.17-21 እግዚአብሔር ፍቅር ነዉ ይላል፡፡ ፍቅር ከእግዚአብሔር ቀዳሚ ባሕርያት እንዱ ነዉ፡፡ ልክ እንደዚሁ እግዚአብሔር እኛንም በፍቅር አቅም አጎልብቶናል/አበልጽጎናል፡፡ ይህን በፍቅር የመሞላታችን ሁኔታ በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠራችን መገለጫ ነዉ፡፡
የእዉነተኛ ፍቅር ምንጭ እግዚአብሔር ራሱ ነዉ፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል ም.3 ቁ.16) ይህ ፍቅር ፍጹም ፍቅር ሲሆን በተቃራኒ የሰዉ ፍቅር ጊዜያዊና ዘለቄታ የሌለዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም ሁል ጊዜ ይህን ፍቅር ልንላበስ ይገባናል፡፡ (1ኛ. ቆሮ. ም.13 ቁ.1)ጀምሮ ፍቅር የእግዚአብሔር ስጦታ ነዉ፡፡ ሮሜ ም.5 ቁ.5፣ ገላተያ ም.5 ቁ.22-26 እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለፀዉ በክርስቶስ ነዉ፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ም.3 ቁ.16 ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነዉ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ተለዋዋጭ አይደለም ወይም በሁኔታች ላይ የተመሰረተ አይደልም፡፡ ሮሜ ም.5 ቁ.8 ነገር ግን ገና ኃጢያተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለዉን የራሱን ፍቅር ያሳያል፡፡ በእግዚአብሔር ፍቅር እንጽና እንላለን፡፡
(ተጨማሪዉን ራዕይ እና ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ይኑረን የሚለዉን መጽሐፍ አንብበዉ ይረዱ፡፡)
          

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!!
  ለተጨማሪ  መረጃ

ዌብሳይት  www.eotc-yemm.info.et


No comments:

Post a Comment